በጎርፍ አደጋ ከ217 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ሲፈናቀሉ 580 ሺሕ ነዋሪዎች አደጋ ተጋርጦባቸዋል

በጎርፍ አደጋ ከ217 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ሲፈናቀሉ 580 ሺሕ ነዋሪዎች አደጋ ተጋርጦባቸዋል
Sep 16, 2020

በአፋር 14 ሺሕ ሔክታር በላይ የደረሰ ምርት ወድሟል

በባህር ዳርና በጋምቤላም ከፍተኛ ጎርፍ ተከስቷል

ሰሞኑን በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎችና 23 ዞኖች በጣለው ከባድ ዝናብ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ 217 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ከቀያቸው ሲፈናቀሉ፣ 580 ሺሕ ነዋሪዎች ደግሞ አደጋው እንደተጋረጠባቸው ተገለጸ፡፡

አደጋው በተለየ ሁኔታ የታችኛው የአዋሽ ተፋሰስ አካባቢዎች ላይ እንደተከሰተ፣ በሔሊኮፕተርና በጀልባ በተደረገ ርብርብ የነዋሪዎች ሕይወት ሳይጠፋ ለማትረፍ መቻሉም ተጠቁሟል፡፡

የሰላም ሚኒስትሯ / ሙፈሪያት ካሚልና የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (/) ሰኞ መስከረም 4 ቀን 2013 .. ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ በርካታ ነዋሪዎች የተፈናቀሉት በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በጋምቤላና በሌሎች ክልሎች ነው፡፡ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ (/) ጎርፉ ከመከሰቱ አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ ባይሰጥ ኖሮ፣ ጉዳቱን መቀነስም ሆነ የሰው ሕይወት ማዳን እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡ 2012 .. የክረምት ወቅት የታየውና አሁንም ቀጥሎ የሚገኘው የአዋሽ ወንዝ ታይቶ እንደማይታወቅም አክለዋል፡፡

በጎርፉ የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍ አስቸኳይና ዘላቂ ተግባራት ተለይተው እየተከናወኑ መሆናቸውን፣ ዜጎች ለከፋ ችግር እንዳይዳረጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጭምር በቅርበት እየተከታተሉት መሆኑን ደግሞ የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ተናግረዋል፡፡ ምግብና የተለያዩ ቁሳቁሶች አደጋው ለደረሰባቸው ዜጎች እየቀረበላቸው መሆኑን ጠቁመው፣ ወረርሽኝና ሌሎች የጤና ችግሮች እንዳይከሰቱ እየተሠራ መሆኑን አክለዋል፡፡

በአዋሽ ተፋሰስ 136 ሚሊዮን ብር 130 ኪሎ ሜትር የጎርፍ መከላከያ ሥራ መከናወኑን ያስረዱት ስለሺ (/) ይበልጥ ይደርስ የነበረውን አደጋ ለመቀነስ ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡ የጎርፍ አደጋን በዘላቂነት ለመከላከል ስትራቴጂካዊ ዕቅድ በማውጣት አጠናክሮ መሥራት አስፈላጊ መሆኑንና ወደ አዋሽ ተፋሰስ በሚገባው የሎጊያ  ወንዝ ላይ ግድብ ለመሥራት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አዋሽ ወንዝ በተለይ በአፋር ክልል በደረሱ ሰብሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን፣ ሰሞኑን 14 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ በነበረና በደረሰ ምርት ላይ ጉዳት መድረሱም ታውቋል፡፡ ከምርቶቹ ውስጥ ሸንኮራ አገዳና ጥጥ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙም ተጠቁሟል፡፡ በእርሻ  ልማት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶችና አርሶ አደሮች ለፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን፣ የአሚባራ መካከለኛ አዋሽ እርሻ ልማት ድርጅት 1.5 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት እንደወደመበት ተገልጿል፡፡ በዚህ ምክንያት 5,000 ያህል ሠራተኞች ሥራ መፍታታቸውም ተጠቁሟል፡፡

በአማራ ክልልም የጣና ሐይቅ ሞልቶ የጎርፍ መጥለቅለቅ በመድረሱ፣ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምሥራቅ ደንቢያ ወረዳ ከአምስት ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በምሥራቅ ደንቢያ ወረዳ አዲስጌ ድጌ፣ ዳብሎና ጣና ወይን ቀበሌዎችም 935 አባወራዎች ተፈናቅለዋል፡፡ ጎርፉ 5,962 ሔክታር ላይ የሚገኝ ማሽላ፣ በቆሎ፣ ሩዝ፣ ጤፍና በርበሬ ማሳ ማውደሙ ተገልጿል፡፡

ሰሞኑን በጋምቤላ በጣለው ከፍተኛ ዝናብ የሞላው ጊሎ ወንዝ ባደረሰው የጎርፍ አደጋ፣ የጁወሩ ወረዳ ነዋሪዎችን ማፈናቀሉ ተገልጿል፡፡ የክልሉ አደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ እንዳስታወቀው 7,339 ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥት ዕርዳታ ካላደረገላቸው ጎርፉ እየጨመረና ከክልሉ አቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን አስታውቋል፡፡

Latest active tenders