የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከሳፋሪኮም-ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጋር የኦፕቲካል ፋይበር ኪራይ ሥምምነት ተፈራረመ፡፡
ሥምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ እና የሳፋሪኮም-ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሚስተር አንዋር ሶውሳ ናቸው፡፡
ሥምምነቱ በመጀመሪያ ምዕራፍ 4097 ኪ.ሜ፣ በሁለተኛው ምዕራፍ 2078 ኪ.ሜ እንዲሁም በሶስተኛው ምዕራፍ 2904 ኪ.ሜ የኦፕቲካል ፋይበር መስመር ኪራይን ያጠቃልላል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ሥምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በጋራ ተባብረው እንዲሰሩ መሠረት የሚጥል ነው፡፡
ተቋሙ ከኃይል ማመንጨት እና ማስተላለፍ ባሻገር የቴሌኮም ዘርፉን ዲጂታል ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡
ሥምምነቱ ለሳፋሪኮም እንደ መልካም ጅማሮ የሚታይ ነው ያሉት አቶ አሸብር የጋራ ተጠቃሚነትን ከፍ የሚያደርግ በመሆኑ ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል፡፡
የሳፋሪኮም-ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሚስተር አንዋር ሶውሳ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ እያሳየች ያለውን አወንታዊ ዕድገት አድንቀው ሥምምነቱ ከተቋሙ ጋር ያለንን በጋራ የመሥራት ፍላጎት የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡
ኩባንያቸው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽኑን ለማሳካት በሚደረገው ርብርብ ውስጥ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የቴሌኮም አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለማቅረብም እየተሰራ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በመጀመሪያው ምዕራፍ የኦፕቲካል ፋይበር መስመር ኪራይ በዓመት እስከ 140 ሚሊዮን ብር ገቢ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እስከ 15 ሺህ ኪ.ሜ የሚሸፍን የኦፕቲከል ፋይበር መስመር ባለቤት ሲሆን ኢትዮ-ቴሌኮም 8745 ኪ.ሜ በኪራይ እንዲሁም ደግሞ ተቋሙ ለውስጥ የመረጃ ልውውጥ እየተጠቀሙበት ይገኛል፡፡